የጀማል ኻሹቅጂ ህልፈት እና መዘዙ

ለሀገሩ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ለንጉሳዊያኑ ቤተሰብ እውነተኛ ታማኝ የነበረ አንድ ታዋቂ ግለሰብ ከሁለት ሳምንታት በፊት የጋብቻ ጉዳዮችን ለመጨራረስ በቱርክ ኢንስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ ቀጠሮ ነበረውና ወደዚያው አቀና። ወደ ኢምባሲው ያመራው የቀድሞ ባለቤቱን የፍቺ ጉዳይ ለመዝጋት እና አዲሷን ቱርካዊት እጮኛውን አስከትሎ ነበር። ግና ቀልጣፋ መስተንግዶና አገልግሎት ይሰጡታል ተብለው ከሚታሰቡ የገዛ ሀገሩ ሰዎች እጅ ላይ ሞት አድፍጦ ጠበቀው። ወደ ቆንስላው እየተራመዱ የገቡት እግሮቹ መልሰው ለመውጣት አልታደሉም። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የትዳር አጋሩ ትሆናለች ተብላ የታሰበችው እጮኛው በሃይል ጮኸች። የየሀገራቱ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን ልሳኖች በሰፊው ተከፈቱ። ካሜራዎች ሁሉ ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ዘመቱ። እያነፈነፉ ያገኙትን መረጃ ለዓለም ጆሮ ለማድረስ ፊታቸውን ቱርክ ውስጥ ካለው የሳዑዲ ዓረቢያ ቆንስላ አዞሩ። ቱርክ «ሰውየው ወደ ቆንስላው ከገባ በኋላ አልወጣም» የሚል መግለጫ ሰጠች። ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ ጀርመን ውስጥ ለሚታተም ጋዜጣ «ጀማል ወደ ቆንስላው ከገባ በኋላ ተመልሶ በፍጥነት ወጥቷል» የሚል መግለጫ ሰጠች።

ሰዎች በሁለቱ ወሬዎች መሐል ዋለሉ። የመጀመሪያው ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በኩል የተሰጠው ኦፊሴላዊ መግለጫ ሲሆን ይኸውም «ጀማል ወደ ቆንስላው ከገባ በኋላ ቆንስላውን በፍጥነት ለቆ ወጥቷል» የሚል ነው። «ለቆ ወጥቷል» ከሚለው ዓ.ረፍተነገር ውስጥ «ለቆ» የሚለውን ቃል በአጽንዖት መመልከት ተገቢ ነው። ትርጉሙን ማሰላሰል ይሻል። ሁለተኛው ደግሞ ከላይ በቱርክ መንግስት የተላለፈው ኦፊሴላዊ መግለጫ ነው። ሰዎች ከዓለም የመገናኛ ብዙኋን ዘገባዎች በመነሳት የቱርክ መንግስትን መግለጫ ሲቀበሉ የሳዑዲ ዓረቢያን ግን አልተቀበሉም። እንዲያም ሆኖ የሳዑዲ ዓረቢያን ዘገባ ተቀብለው የቱርክን ለመቀበል ያመነቱም አልታጡም። በጠንካራ መረጃ የተደገፈው ዘገባ የቱርክ ሲሆን የሳዑዲ ዓረቢያ ግን ቀውሱ ሲጀምር አንስቶ ደካማ ነበር። አሁን መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ «ሳዑዲ ዓረቢያ ዘገባውን ያመነችበት ምክኒያት ምንድን ነው?» የሚለው ነው። በዓረቡ እና በሙስሊሙ ዓለም ያለው የአስተሳሰብ ካርታ (Thinking Map) በጣም አስገራሚ ነው። ይህ የአስተሳሰብ ካርታ የተፈጠረው እውነትን ነጻና እና ጥገኛ ካልሆነ የመረጃ ምንጭ ከማጣት የመነጨ ነው። በዚህም ምክኒያት አንዳንድ ሰዎች የጋዜጠኛ ኻሹቅጂን ጉዳይ የያዙት በባርነት መንፈስ ዓይነት ነው።

አንደኛው ምድብ

ይህ ምድብ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ጥምር ኃይል የመሰረቱ ሀገራት የተዋቀሩበት ሲሆን ፈታኙን ጊዜ ያሳለፉት በሽብር እና ጭንቅ ተውጠው ነው። አደገኛና አስከፊ ተሞክሮዎችን ያሳለፉባቸው ቀናት ብዙ ናቸው። ሚዲያዎቻቸው እውነት ፊት ለመቆም ሰንፈዋል። ስብስቡ የተወከለው በግብፅ እና ዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ ነው። እነዚህ ደግሞ የጥምር ኋይሉ ቁንጮ ሀገራት ናቸው።

ሁለተኛው ምድብ

የሳዑዲን ሩዝ አሰፍሰፍው የሚጠብቁ ሀገራት ናቸው። ከሳዑዲ በኩል የእንጀራ ገመዳቸው እንዳይበጠስ በር ላይ በጭንቅ ተውጠው በመቆም ይታወቃሉ። ሩዙ እየቀነሰ ያለበት ተጨባጭ ሁኔታ ነው ያለው። ባልተለመደ መልኩ የሩዙ ምንጭ እየደረቀ ነው። እንዲህም ሆኖ በታሪክ በጭካኔው አደገኛ ከሚባሉት ሰዎች ተርታ የሚሰለፈውን መሪ ለመደገፍ በዓረቡ እና በሙስሊሙ ዓለም ያሉ ድሃ ሀገራት ውድድር ላይ ናቸው።

ሶስተኛው ምድብ

በዚህ ካቲጎሪ የሚካተቱት ከታሪክ ገጽ ውጭ የሚኖሩ «ዱዓቶች» ናቸው። ለሁለት ምክኒያት ሲሉ በምድሪቱ የሚከናወኑ ክስተቶችን ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ያህል አያውቁም። አንድም አልፎ አልፎ ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚደርሳቸው ቴምርና ሩዝ እንዳይቋረጥ በማሰብ ሲሆን ሁለትም የአላህን ቤት ከመጎብኘት እንዳይከለከሉ በመስጋት ነው። አንዳንዶቹ ድንበር ያለፈ የዋህነት ያጠቃቸዋል። በዚህም ምክኒያት ሳዑዲ ዓረቢያ መጨረሻ ላይ በሰጠቸው መግለጫ ብርክ ይዟቸዋል።

አራተኛው ምድብ

በዚህ ምድብ የሳዑዲ ዓረቢያ ታላላቅ የሐይማኖት ልሂቃን ይገኛሉ። ከተቀመጡበት ቦታ አንጻር በንግግርም ሆነ በተግባር ለእውነት የወገኑ እና የቀረቡ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ አካላት ናቸው። እንደ ደረጃቸው ትልቅነት ለቃላቸው ታማኝና የማያወላውሉ ናቸው የሚል ተስፋ በብዙኋኑ የሚጣልባቸውም ነበሩ። ግና ለሁለት ሳምንታት በዝምታ ተሸበቡ። አንደበታቸው እውነት ለመናገር ታቀበ። መጨረሻ ላይ ግን ከእውነት ውጭ ተነፈሱ። የመንግስትን ኦፊሴላዊ መግለጫ ጠበቁ። ምድር ላይ የተሰጣቸው እንደራሴነት ለአላህ እንጂ ለገዢው መደብ አልነበረም። በዚህ መንገድ የሚያስቡ የሐይማኖት አባቶችን በውስጧ ስለያዘች «ኡማ» ማሰብ እጅግ ያሳዝናል። በዚህም መሰረት የሐይማኖት ሊቃውንቱ በብዙኋኑ ምዕመናን ዘንድ ያላቸው ክብር የወረደበት ተጨባጭ ተስተውሏል።

አምስተኛው ምድብ

በዚህ ስብስብ የተካተቱት ያለ መርህ የሚንቀሳቀሱ ምሁራን ናቸው። ሚናቸው ፖለቲካዊ ሳይሆን ለሰው ልጅ መብት ጥብቅና መቆም ነበር። ለመርህ ተገዢ ያልሁኑ ምሁራን በሟቹ ጋዜጠኛ ጉዳይ ኦፊሴላዊ መግለጫ መጠበቅ አለብን በማለት አንገራገሩ። ከዚህ በፊት ለመግለጽ እንደሞከርኩት ምሁር ብሎ ማለት በአንድ ክስተት ውስጥ ታጥሮ የሚኖር ወይም የመንግስትን ውሳኔ እንዲሁ የሚቀበል ማለት አይደለም። እውነተኛ ምሁር ብሎ ማለት ሰዎች የሚያውቁትን ነገር የሚከትብ ሳይሆን ከመድረኩ ጀርባ ያለውን ሚስጥር ሙያውን መሰረት አድርጎ መግለጥ የሚችል ነው።

ስድስተኛው ምድብ

በሙስሊሙ ዓለም ሐይማኖታዊ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሙሐመድ ቢን ሰልማን ጋር በቅርበት መስራት ወሳኝ ነው ብለው የሚያምኑት የዩናትድ ስቴትስ የቀኝ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ናቸው። ሟቹ ጋዜጠኛ ኻሹቅጂ ሙሐመድ ቢን ሰልማንን የአያቱ ቅጂ ሲል ይገልጸዋል። የተትረፈረፈ የሐብት ጸጋ ባለቤት የሆነች ሐገር ለመምራት ዙፋን ላይ የተሰየመ። በሰለጠነው ዓለም ዘመናዊ ሐገር ለመምራት የሚያስችል እውቀት የሌለው የጎሳ መሪ። ምዕራባዊያኑ «ወጣቱ የለውጥ ሐዋሪያ» እያሉ ያሞካሹት ግልብና ፍሬ አልባ ሰው። ይህ ሰው ለቀኙ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ሁነኛ ሰው ነው። ቡድኑ ደግሞ አሁን ላይ በተለየ መልኩ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል ሙሐመድ ቢን ሰልማንን ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።

ሰባተኛው ምድብ

በዚህ ጭፍራ የሚካተቱት ደግሞ ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን በማድረግ እና «በማጭበርበር» የተካኑ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። ከነበሩበት ቦታ ከፍ አይሉም። የሚያስተላልፉት መልዕክት በውስጡ ያዘለውን ትርጉም በወጉ አይገነዘቡም። ከነዚህ መካከል ተወዳጁ ሸይኽ አብዱረህማን አሱደይስ ዋነኛው ተቃሽ ናቸው። በእስልምናው ዓለም የመንግስት ልሳን እስከመሆን የደረሱ መስለዋል። ከሁለት ቀን በፊት ያለፈው ጁሙዓ በመስጂደል ሐራም ውስጥ ሚንበር ላይ ያሰሙት ኹጥባ በብዙኋን ዘንድ አግራሞትን ያጫረ ነበር። ሙሐመድ ቢን ሰልማንን «ወጣት፣ የለውጥ ስሜት በውስጡ የሚንቀለቀል፣ በምላሱ እና ቀልቡ ላይ አላህ እውነትን ያኖረለት፣ እውነት ተናጋሪ እና በሐቅ የሚያስተዳድር» በሚሉ ቃላት ገልጸውታል። አነኝህ የቃላት ድርደራዎች የሚያመለክቱት ሸይኹ የሚናገሩት ነገር ያለ ማስተንተን መሆኑን ነው። ሰውየው በዕድሜ ወጣት፤ የዙፋን ፍቅሩም እንዲሁ የጋለ ሊሆን ይችላል። ግና « በምላሱ እና ቀልቡ ላይ አላህ እውነትን ያኖረለት ፣ ሐቅ ተናጋሪ እና በሐቅ የሚያስተዳድር » ለሚለው ገለጻ የጎመን ዘር ፍሬ የምታህል ማሰቢያ አቅል ላለው ሰው የሚዋጥለት አይደለም።

ግራ የተጋባው የሳዑዲ ዘገባ እና ወጥነት ያለው የቱርክ ዘገባ

የቱርክ መንግስት ያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎች ጉልበት ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ የገለጻ ጥበብ ፣ የቃላት መረጣ፣ የንግግር ጮሌነት፣ የአነጋገር ስክነት እና ማስተዋል የተንጸባረቀበት እንደነበር ብዙኋኑ አስተውለዋል። በታቃራኒው የሳዑዲ መንግስት መግለጫዎች ደካማ ከመሆናቸውም ባሻገር ገለጻዎቹ በማንገራገር ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ከፖለቲካዊ ጮሌነትም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። የቃላት መረጣ ላይ እንከናማ መሆናቸው ተስተውሏል።

ወጣቱ አልጋወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን በሐገሪቱ ሰፊ የፖለቲካ ልምድና ተሞክሮ ያካበቱ የፖለቲካ ሰዎችን ከሜዳው ላይ በጨለማ በመጥረግ ልምድም ሆነ ሙያ የለሽ የወጣት ቡድኖችን ወደፊት አመጣ። ሐገር መምራት ጨዋታ እና ጊዜ ማሳለፊያ አድርገው የሚቆጥሩ ጠግበው ያልጨረሱ ወጣቶችን ሾመ። ሐገሪቱ ለዘመናት በስልጣን ላይ ከነበሩ ቀሪ ሲኒየር የንጉሳዊያን ቤተሰብ ልጆች ሰፊ ልምድና ተሞክሮ መጠቀም አልቻለችም። ግና ቱርኮች ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ሙያዊና ተቋማዊ አሰራርን ተከትለው ነበር።

ቱርክ በጉዳዩ ዙሪያ ትክክለኛ መረጃዎችን አወጣች። ጉዳዩን ለመግለጽ የተጠቀመችበት ዘዴ ከአንድ ታላቅ ሀገር በሚጠበቅ ቋንቋዊ ለዛ የተደገፈ ነበር። የዓለም ማህበረስብን ትኩረት ሳበች። ቀስ በቀስ ሙያዊ በሆነ መንገድ የምትለቃቸው መረጃዎች ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ አመለካከት እንዲፈጠር ማድረግ የሚያስችል ስኬታማ ስራ አከናወነች። አስገራሚው ነገር የሚወጡት መረጃዎች ውስጣቸው እንግዳ በሆኑ ነገሮች የተሞሉ ነበሩ። በጥንቃቄ ከመገለጻቸውም በላይ አሳማኝ ለመሆን የሚያስችል ሚዛን ደፊ ቅመም ነበራቸው። ከቱርክ የመረጃ እና ዘገባ አቅም አንጻር የሳኡዲ ዓረቢያው ዘገባ «የቲም» ሆነ። ከቱርክ የመረጃ አቅም ፊት ለመቆም ደኸየ። በዚህም ምክኒያት «ዜጋችን ከቆንስላው (ወጥቷል) እና ከቆንስላው (ለቆ ወጥቷል) በሚሉ ገለጻዎች ብቻ ተወሰኑ። የሁለተኛው ገለጻ ጤናማ ይመስላል። ምክኒያቱም የሙሐመድ ቢን ሰልማን አፋኝ ቡድኖች የሐገር መሳሪያዎችን እና ቢሮዎችን በመጠቀም ለሐገር ክብር የሆኑ ዜጎችን ለመግደል ደንታ የላቸውምና።

የቱርክ ዘገባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ሀገራት እና በተለይም በዓረቡ ዓለም ከፍተኛ ትኩረት አገኘ። ለዚህም ነው ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸውን (ፖምፒዮን) ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ቱርክ እንዲያቀኑ ያደረጉት። የፖምፒዮ አመጣጥ ለጉብኝት ሳይሆን ትዕዛዝ ሰጪ እና ከልካይ ሆነው ነው። ሳዑዲ ዓረቢያ የሆነ ነገር እንድታወጣ ጠይቋል። ምናልባት ጥያቄው ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል።

ሳዑዲ ዓረቢያ አዲስ መግለጫ አወጣች። ነገር ግን መግለጫው የሙሐመድ ቢን ሰልማንን የግንዛቤ እጥረት አጉልቶ ያሳየ ነበር። የአሜሪካ ጋዜጦች ወሬውን «በትራምፕ እና በዙሪያው ካሉ ሰዎች ብቻ ቢሆን እንጂ በሌሎች ተቀባይነት የሌለው» በማለት በጽኑ አውግዘውታል። አሜሪካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ ዘገባውን «ከአይምሮ ጋር የሚጋጭ» ብሎታል። እዛ ያለው አይምሮ ከጥቅም ጋር የተቆራኘ ሳይሆን ነጻ ሆኖ የሚያስብ ነው። ዘገባው ሁለት ነውሮች አሉት። የመጀመሪያው ነውር ክስተቱን ወደ ሰዎች ጆሮ ለማድረስ የተመረጠበት መንገድ ነው። «በጋዜጠኛ ጀማል ኻሹቅጂ እና በቆንስላ ሰራተኞቹ እንዲሁም መርማሪዎቹ መካከል ጸብ ተነሳ» የሚል ነው። የጉዳዩ አስገራሚ ነገር መርማሪዎቹ ከመነሻው ለጸብ ዝግጁ ሆነው የመጡ መሆናቸው ነው። በጭካኔ የተሞላ ግድያ የሚፈጽሙበትን መሳሪያ አንግበው የሔዱ ናቸው። በዚህም ምክኒያት የአንድ ዜጋ ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ ጠፋ። ሁለተኛው እንከን የጋዜጠኛው ጀማል ኻሹቅጂ አስክሬን የት እንዳለ ካለመታወቁም በላይ አስክሬኑን እንዲያስወግድ ተልዕኮ የተሰጠው የቆንስላው ሹፌር ለቱርካዊ ዜጋ እንዳስረከበ አድርጎ መዘ፟ገቡ ነው።

ከዚህ በፊት በትንተናዎቼ እንደገለጽኩት መሰል ዘገባዎችን ስትመለከቱ የሳዑዲ ባለስልጣናት ልባቸው «በህንድ ፊልም» የተመታ መሆኑን ይጠቁማል። የተሰራው እጅግ በጣም አስቀያሚና ቀሽም ፕሮዳክሽን ነው። መደበኛ ከሆነው ቂልነት የወጣ መሆኑን አመላካች ነው። የሳዑዲን መግለጫ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፉ ጋዜጦች በሙሉ በሚባል መልኩ አንድ ቃል እየተነፈሱ ነው። ምጸት ፣ ስላቅ ፣ ምጸት …ስላቅ …ምጸት

የዘገባው ቅርጻዊ ነውር ከይዘቱ አንጻር ምንም ማለት አይደለም። መግለጫው ከዱባይ እና ከካይሮ ስለተነሱት ሁለት አውሮፕላኖች ምንም ያለው ነገር የለም። ሁለቱም የጥምር ጦሩ አባል ሀገራት መሆናቸውን ልብ ይሏል። በተጨማሪም ቁጥሩ በዛ ያለ የጸጥታና ደህንነት ቡድን እንዲሁም በግድያ ሙያ የተካኑ ሰዎች በዚህ መልኩ መንቀሳቀሳቸው ትክክለኛ ዓለማው ምን እንደነበር መግለጫው አልጠቆመም። የወንጀሉ ድራማ የተፈጸመበት ቦታ ላይ ፋናውን ለማጥፋት የተደረገው ጥረትም አልተገለጸም።

ከወሬው ሁሉ አስቂኙ አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን የተፈጸመውን ጉዳይ በተመለከተ ምንም የሚያውቀው መረጃ እንደሌለ እና ወንጀሉ የተፈጸመው በስህተት እንደሆነ አድርጎ መቅረቡ ነው። ነገር ግን የአልጋ ወራሹ ጽ/ቤት አማካሪ የሆነው ሱዑድ አልቀህጧኒ ከስራ መባረሩ ከተጋለጠው የሙሐመድ ቢንሰልማን የድራማ ክፍል አንዱ ነው።

የሳዑዲ ባለስልጣናት ለሁለት ሳምንት በዝምታ ተሸበቡ። ወዝ ካለው የቱርክ መረጃ ፊት አንዲት ቃል ከአንደበታቸው ለመተንፈስ አንገራገሩ። መውጫ ቀዳዳ አጡ። ስርዓቱ ካጋጠመው አስጨናቂ ጊዚያት ይህ ወሳኙ ነው። መረጃዎች ከቱርክ በየቅጽበቱ በሚፈነዱበት ተጨባጭ የሳዑዲ ባለስልጣናት ዝምታ ተቀባይነት አጣ። ሁሉም አዳዲስ መረጃዎችን ለመስማት እና ለማየት ጆሮ እና አይኑን በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ተክሏል። ቱርኮች በመረጃ ጉልበት የበላይ ሲሆኑ የሳዑዲ ባለስልጣናት ከፊታቸው አስቸጋሪ ጊዜ ተጋረጠባቸው። የዚህ ሁሉ ምክኒያት የፊልሙ ፕሮዳክሽን መክሸፉ ነው። የቀረው እንቆቅልሽ «ከዚህ አጣብቂኝ መውጫ ቀዳዳው ምንድን ነው ?» የሚለው ነው።

ከገባበት ቅርቃር መውጫ የሚሆነው ብቸኛ መፍትሔ በዶናልድ ትራምፕ በኩል ብቅ አለ። ትራምፕ ከአልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካለው እና አማቹ ከሆነው ኮሽነር (የኢቫንካ ባለቤት) የተሰጠውን ምክር ከልብ ሰማ። ቢሆንም ትራምፕ የሚመራው በአደረጃጀቱ ጠንካራ የሆኑ ተቋማት ያላትን ሀገር ነው። በዙሪያው አንቱታን ያተረፉ ህግ አውጪዎች እና ትንፋሽ የማያሳልፉ ጠንከራ ሚዲያዎች አሉ። ጫና መፍጠር የሚችል የህዝብ አስተያየትም እንደ ዋዛ አይታይም። እንዲህም ሆኖ ትራምፕ ሙሐመድ ቢንሰልማንን ለመከላከል የሚጠቀምበት የፖለቲካ ካርድ በፖምፒዮ በኩል መዘዘ። ካርዱ በቅርጽም በይዘትም ደካማ ነበር። በዚህም ምክኒያት ተሸብቦ የነበረው የሳዑዲ ከናፍር ተከፈተ። ጀማል ኻሹቅጂ መገደሉን በይፋ አመኑ።

በሸይኽ አብዱረህማን በሺር [ በመሀመድ አህመድ ተፃፈ]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *