ኢትዮጵያ የባህር ሀይል ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምራለች፡

ባህር ሃይሉን እንደገና ለማዋቀር አደረጃጀቱና አቋሙን ለመወሰን እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የጦር ሀይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ናቸው፡፡

ጄኔራል ብርሃኑ የባህር ሀይሉ እንደገና የመዋቀሩን አስፈላጊነት አብራርተውል፡፡

የኢትዮጵያ ጥቅም የሚመላለስባቸው የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ከ60 ኪሎ ሜትር ቅርበት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ በባህሩ ላይ የሚኖራትን ጥቅም ለማስከበርም፣ የባህር ሀይል መቋቋም አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ተናግረዋል፡፡

የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ በአካባቢው ተፅዕኖ የማሳደር አቅሟን ለማጎልበትና፣ በቀጠናው ቀውስ ቢፈጠር በባህር ሃይል እጦት ተጎጂ ላለመሆን ብርቱ፣ ጠንካራ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና መሳሪያ የታጠቀ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል እንደሚገነባ ጄኔራል ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ሃገሮች በኤርትራ፣ በሶማሊያ፣ በፑንትላንድ የጦር ሰፈር ይዘው ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን የጠቀሱት ጄኔራል ብርሃኑ “ኢትዮጵያ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ሃገር ነች በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ባህር አስቀምጠን የብስ ላይ ብቻ ተገድበን የምንቀመጥበት ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡

የባህር ሃይል የጦር ሰፈሩንም በባህር ዳርቻዎቹ ከሚገኙ ሃገሮች ማግኘት እንደሚቻል ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የባህር ሃይል መፈራረሱ እንደ ሃገር አሳዛኝና የሚያፀፅት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጄኔራል ብርሃኑ እጅግ ብርቱ፣ ጠንካራና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሳሪያ የታጠቀ የሚሉትን የባህር ሀይል ለማደራጀት በሚደረገው እንቅስቃሴ አቅም ያላቸውን የቀድሞ የባህር ሃይል አባላት እንደሚሳተፉ ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለ መጠይቅ አረጋግጠዋል፡፡

ምንጭ: ሸገር ራዲዮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *