የቀድሞ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ ተጨማሪ 14 ቀናት ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ሙሀመድ ኡመር ላይ ለሚያደርገው ምርመራ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ቀን ተፈቀደለት፡፡

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ የያዘለትን የአቶ አብዲ ጉዳይ ተመልክቶ እና ከወንጀሉ ክብደትና ውስብስብነት አንፃር ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ ትክክለኛ መሆኑን አምኖበታል፡፡

ፖሊስ ካለፈው ቀጠሮ ወዲህ 16 ገፅ የኦዲት ማስረጃ ማቅረቡን በንግድ ተቋማት ላይ የደረሰን ጉዳት የሚገልፅ 35 ገፅ ማስረጃም አቅርቤያለሁ ብሏል፡፡

ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የፈለገው በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች 200 ግለሰቦች መገደላቸውን በተጠርጣሪዎቹ ምርመራ ማግኘቱን ፖሊስ አመልክቶ በጅምላ የተቀበረውን አስክሬን የመለየት ስራና ምስክር ለመቀበል ለወንጀሉ ተግባር የዋለ ገንዘብ እና መሳሪያ ለመያዝ እንዲቻለው መሆኑን አመልክቷል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች 200 ሰዎች ተገደሉ የተባለው አዲስ ምርመራ ስለሆነ ብቻውን ተነጥሎ ሊታይ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎች አደረሱት የተባለው ጉዳትም በዝርዝር ሊቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡

በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት ተጨማሪ ፈቅዶ ለህዳር 13, 2011 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ: ሸገር ራዲዮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *