የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አቶ ኡሞድ ኡጁሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ

የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ አቶ ኡሞድ ኡጁሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንኳይ ጆክን ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ፡፡

ምክር ቤቱ አዲስ ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሾመው የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት እና ምክትላቸው አቶ ሰናይ አኩዌር ያቀረቡት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ነው።

የቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ እንዳሉት ላለፉት ስድስት ዓመታት ክልሉን በመሩበት ወቅት የተመዘገበው ዕድገት የክልሉን ገፅታ የቀየረ ቢሆንም ለውጡ ውስንነት ነበረው፡፡

በተለይም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ለመጣው የክልሉ ህዝብ የልማት ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለመቻሉ በኃላፊነት ዘመናቸው ከታዩት ቁልፍ ችግሮች ዋንኛው መሆናቸውን አቶ ጋትሉዋክ ጠቅሰዋል፡፡

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ስልጣን የህዝብ እንደመሆኑ የኃላፊነት ቆይታ የሚወሰነው በህዝብ ነው ያሉት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤቱ የቀረቡለትን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄያቸውም ከ1 ድምፀ-ተአቅቦ በስተቀር በሙሉ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

አቶ ጋትሉዋክ በአገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መሰረት ኃላፊነታቸውን ያለምንም ተፅዕኖ ለተተኪ አመራር ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክረው በማስቀጠል የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ተተኪዎቹን አመራሮች አደራ ብለዋል፡፡

አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ወቅቱ በክልሉ ብልሹ አሰራር እንደችግር ጎልቶ የወጣበት መሆኑን ጠቁመው የክልሉ ህዝብ ከአዲሱ አመራር ጎን በመሰለፍ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር አዲሱ አመራር በቀጣይ በክልሉ አገልግሎትን ለማሻሻል፣ ሰላምን ለማስፈን፣ የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና እየተከናወነ ላለው በመንደር የማሰባሰብ ተግባር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የቀድሞዎቹ አመራሮች በኃላፊነት ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋፅዖ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንደተበረከተላቸው የጋምቤላ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

ምንጭ: www.fanabc.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *