የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሊውለበለብ ነው

የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር እንዲውለበለብና መዝሙሩም እንዲዘመር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንደገለፁት የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደቡብ አፍሪካ ሲከበር አባል አገራቱ የአፍሪካ ህብረትን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያውለበልቡ ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እስካሁን ተግባራዊ ሳታደርግው ቆይታለች ብለዋል፡፡

ከአባል አገሮች መካከል ናሚቢያ እ.ኤ.አ ከ 1998 ጀምሮ በመንግስት ተቋማቷ የአፍሪካ አንድነትን ኋላም የአፍሪካ ሕብረትን ሰንደቅ ዓላማ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዋ ጎን ለጎን በማውለብለብ ቀዳሚ መሆኗን እና እ.ኤአ 2015 ጀምሮ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ መከተሏን አቶ መለስ አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያም እንደ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መሥራችና መቀመጫ አገር በመሆኗ የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጎን ለጎን ለማውለብለብ የሚያስችል ረቂቅ በማጋጀት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

ብሄራዊ መዝሙሩ እንዲዘመር በማድረግ ቅድሚያ መውሰድ እና ለሌሎች አብነት መሆን ይገባታልም ብለዋል አቶ መለስ ዓለም በመግለጫቸው፡፡

ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡

አፍሪካውያን ኢትዮጵያን እንደቤታቸው እንዲቆጥሩ በቦሌ አለም ዓቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩም ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡- EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *