በአፍሪካ ብስክሌት ዋንጫ ኢትዮጵያውያን የብርና የነሀስ ሜዳሊያ አገኙ

በኤርትራ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ብስክሌት ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን የብስክሌት ተወዳዳሪዎች የብርና የነሀስ ሜዳሊያዎች አስመዘገቡ።

በአስመራ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ የብስክሌት ዋንጫ ውድድር በተለያዩ ደረጃዎች ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ሶስት የነሀስና ሶስት የብር ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችለዋል።

በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የክሮኖሜትር የወንዶች ውድድር ኢትዮጵያ የሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ ኤርትራ ወርቅ እና ሩዋንዳ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በሴቶች ውድድር ደግሞ ኤርትራ ወርቅ፣ኢትዮጵያ የብር እና ደቡብ አፍሪካ የነሃስ ሜዳሊያ አሸንፈዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው በሴቶች የአዋቂዎች ውድድር ከኤርትራ አድያም ተስፋአለም ወርቅ፣ ከኢትዮጵያ ምህረት አስገደ ብርና ከደቡብ አፍሪካ ሊኤዜል ጆርዳን የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።

ከ23 ዓመት በታች የሴቶች ውድድር ኤርትራ የወርቅ ሜዳሊያ ስታስመዘግብ ኢትዮጵያ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ የግሏ ማድረግ ችላለች።

በተመሳሳይ በወንዶች ከ23 ዓመት በታች ውድድር ኤርትራ የወርቅና የብር አሸናፊ ስትሆን ኢትዮጵያ የነሃስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።

ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው በዚህ የብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ግብፅ፣ሩዋንዳ፣ናይጀሪያ፣ ሲሸልስ፣ቤኒንና ደቡብ አፍሪካ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ምንጭ፦ ኢ.ፕ.ድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *